top of page

ጥቂት ዕውቀት

ጥቂት ዕውቀት በደል አይደለም፣ ትንሽ ትምህርት ኃጢዓት አይደለም፡፡ ጥቂት ዕውቀት አደገኛ የሚሆነው ተጨማሪ ለማወቅ ካላነሳሳ፤ የበለጠ ለመማር ካላነቃቃን ነው፡፡ ከሃይማኖት እስከ ፖለቲካ፤ ከቤተ ክህነት እስከ ቤተ መንግስት እታዘባለሁ፡፡ የጥቂት ዕውቀትን መልካም እድልነት ሳይሆን አደገኛ ተፅዕኖን ባለመረዳት ብዙ የማይጠቅሙ ነገሮች ሲሆኑ አያለሁ፡፡ የጥቂት ዕውቀት አደገኛነት ምንድነው?

# ለፍርድ ያስቸኩላል

ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ በማብጠልጠል የበታችነት ስሜትን ያውጃል፡፡ በዘመናቸው አንዲት ጠብታ ለሀገርም፤ አልያም ለህዝብ፤ ወይም ለሌላው የሚሆን ነገር ጠብ ያላደረጉ ሰዎች፤ እንደ አቅሙ ሊሰራ የሚውተረተረውን በምላስ ቢላዋ ይከትፉታል፡፡ አስተምረው አላየናቸውም፤ ሰባኪን ከፍ ዝቅ ሲያደርጉ ልክም የላቸው፡፡ ፅፈው አላበረከቱም፤ የፀሐፍያንን ቅስም ለመስበር ከአቦ ሸማኔ ይፈጥናሉ፡፡ መርተው አላየንም፤ መሪን ሲያኮስሱ ተካካይ የላቸውም፡፡ የሚሰድቧቸው ሰዎች ባይኖሩ፤ ህይወት አይኖራቸውም፤ ህይወታቸው ስድብ ነውና፡፡

ካለችን ዕውቀት ወጣ ብለን ለማየት ዝግ መሆን፤ በተወለድንበት አልጋ፤ በታዘልንበት አንቀልባ መሞት. መደምደም ማለት ነው፡፡ ዓለም እጅግ ሰፊ ናት፤ ያልደረስንበት እውቀት፤ ያልሰማነው አስተሳሰብ፤ ያልዳሰስነው አድማስ እጅግ ብዙ ነው፡፡ በልጅነት ሩቅ የሚመስለን ሰፈርና አገር ዛሬ ስናድግ በደቂቃዎች የምንደርስበት ሆኗል፡፡ ለምን ቢባል አድገናልና፡፡ በትንሽ ዕውቀት መቆየት፤ ትንሽዋን ትልቅ አድርጎ የትልቅን ክብር ይጋርደናል፤ ሁሉን ያወቅን መስሎን ያችን ትንሽ መንደር አግዝፎ ዓለምን የጨበጥን አስመስሎ የዓለም መሳለቂያ ያደርገናል፡፡ ተመልከቱ፤ ዳቦ በማይሆን፤ ረሃብተኞችን በማያተርፍ እንቶ ፈንቶ ስንፋጅ የምንውል ገራሚዎች ሆነን የቀረነው ለዚህ ነው፡፡ ቀድመን ጀምረን በጀመርንበት እንኳ መቆየት ያቃተን ለዚህ ነው፤ ወደ ፊት መጓዙ ቀርቶ፡፡

#ያለ እኔ ያሰኛል

እኔ ካልፃፍኩት፤ እኔ ካልፖተለኩት፤ እኔ ካልሰበኩት፤ እኔ ካልዘመርኩት፤ እኔ ካለተስማማኝ፤ እኔ ካላፀደኩት ያሰኛል ትንሽ ዕውቀት፡፡ በክርስትናው ሜዳ እንኳ ትናንት በአንድም በሌላ መንገድ መገፋት የደረሰባቸው ሰዎች፤ ዛሬ ነገር ለይቶለት ነፃ ሆነው ራሳቸውን መግለፅ ሲችሉ መፋጀት መጀመራቸው፤ ትናንት አንድ አድርጎ ያቆያቸው አቋማቸው ወይም የዓላማ አንድነታቸው ሳይሆን፤ የጋራ ጠላት መኖር እንደሆነ እንታዘባለን፡፡ የጋራ ጠላት ሳይኖር ዋናው ጠላት እኔነት በትንሽ ዕውቀት ታጅቦ መድረኩን ያዘ፡፡ በፖለቲካውም እንዲሁ ነው፡፡ በመንግስት ላይ ተቃውሞ ሲያሰዉ አንድ የመሰሉን፤ በግል ሲገናኙና ሲገለጡ ጭብጥ ዕውቀታቸውን በወራት አራግፈው መለመላቸውን አየናቸው፡፡ በስልጣን ያሉም በበታች ያሉም እኩል ሲናገሩ፤ ልጅ ከአዋቂው ንግግሩ አልለይ ሲል ታዘብን፡፡ እኔ ያልወጠወጥኩት ስንል፤ ከወጥ ሌላ ስንቱ ምግብ አመለጠን

#ውስጥን ይጨርሳል

በጥቂት ዕውቀት ተጠምደው፤ እንደ ልበ ደንቆሮ በሰሙት አዲስ ነገር የሚያብዱ ሰዎች፤ ዘልባቸው እስከፊታቸው መጨማተር ይጨርሳቸዋል፡፡ በነቀፋ እና ስድብ የተጠመዱ ሰዎች ውስጣቸው በማይነቀል ደዌ ይነቅዛል፤ ሰላም አይኖራቸውም፡፡ አእምሮአቸው በአዲስ ዕውቀት አይለመልምም፤ በዚያች በሚያውቋት ዕውቀት ታስረው ሳያድጉ ይቀነጭራሉ፡፡ ከራሳቸው መጠውል አልፎ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች የተሰጣቸው ነፃነት ተጠቅመው እንዳይለመልሙ ያንቋቸዋል፡፡ ሁሌም አሉታን የሚያስተናግድ አዕምሮአቸው ተለየ ነገር መፍጠር፤ ማበርከት ይሳነዋል፡፡

ወዳጆቼ ትንሽ ዕውቀት በደል አይደለም፤ ትንሽ ዕውቀት ለትልቁ ካዘጋጀን በረከት ነው፡፡ አለማወቃችን የበለጠ ለማወቅ ካነቃን ህይወት ገብቶናል፤ ጉዞውን ጀምረናል፡፡ ራሳችንን ከፍት እናድርግ፤ የሌሎችን ሀሳብና ነጻነት እናክብር፤ ዛሬ ምን ተጨማሪ ነገር አወቅሁ፤ ምን ተማርኩ እንበል፡፡ መነዳደፍ ትርፉ እልቂት ነው፤ እንንቃ፤ ዓለም ሰፊ ናት!!!

bottom of page