top of page

ራሳችሁን አታቃጥሉ

የፅሑፌ መነሻ ሰሞኑን ከወደ ጂግጂጋ የሰማነው አብያተ ክርስቲያናትን የማቃጠል መርዶ ነው፣ ዜና ብቻ ልለው አልሻም፡፡ ስለ ቃጠሎው እኩይነት እና አሳፋሪነት ለመናገር የተጠቂው ወገን አካል መሆንና አለመሆን መስፈርት ነው ብዬ ፈፅሞ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ፣ ከዚያም በላይ ሰው ስለሆንን ነው፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ማለት፣ በተለይም በኢትዮጵያ፣ የጥበብ እና የትምህርት መካናት፣ የታሪክና የባህል ህያው ሀውልቶች፣ የኢትዮጵያ ማነነት የተሸመነባቸው፣ ዜጉችን ስነ ምግባር እና የሀገር ፍቅር ሚያስተምሩ ስፍራዎች ናቸው፡፡ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያ አለች፣ ትውልድ አለ፣ የሀገር ነገም እንደዚያው፡፡ ስለዚህ አንድ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሰው የትኛውንም የሀይማኖት ተቋም ሲያቃጥል፣ ራሱን እያቃጠለ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በእነዚህ ተቋማት ታርቆ እና ታርሞ ያላደገ ትውልድ ነገ ራሱኑ ቀርጥፎ የሚበላው ስለሆነ ነው፡፡ ምናልባት ዛሬ የምናያቸው የሃይማኖት ተቋማት በመሪዎቻቸው ችግር ዝቅጠት ውስጥ ገብተው ቢሆን እንኳ፣ ሰው ቋሚ አይደለምና በዚህ ልናመካኝ አይገባም፡፡ ደጎቹን እንዳየን፣ ከክፉዎቹም ልንማር አለንና፡፡

ሰው ነፃ ፍጥረት ነው፡፡ የፈለገውን የማመን ያልፈለገውን ያለማመን መብቱ ሊከበርለት የተገባ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ከእምነቱ የተነሳ ለይቶ ማጥቃት፣ በተለይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የለየለት ውድቀት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በህዝቡ ዘንድ ከሚታወቁት ኦርቶዶክስ፣ እስልምና፣ ፕሮቴስታንት፣ ዋቄፈታ፣ ካቶሊክ ጀምሮ ብዙዎቻችን ያላጠናናቸው፣ በሩቅ ስፍራ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚከተሏቸው እምነቶች አሉ፡፡ በምንም ለማያምኑም ቢሆን በምንም አለማመናቸው ለእነርሱ እምነት ነው፡፡ ሁሉም እኩል ነፃነት. እኩል መብት ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ሁሉም የእኛ፣ ሁሉም ሰዎች ናቸው፡፡ ታዲያ ማቃጠልን መፍትሄ አርገን እንዘልቅ ይመስላችኋልን? በጭራሽ፡፡ ደግሞኮ ቤተሰባችንን እንኳ ብናይ የሀይማኖቱ ጉዳይ ዥጉርጉር ነው እኮ፡፡ ታላቅ እህቱ የእንትን ሀይማኖት ተከታይ ሆና፣ አጅሬው ደጅ ባለው ላይ አካኪ ዘራፍ ይላል፡፡ እንረጋጋ፣ ሰው በሰውነቱ ይከበር!!

ድርጊት በሀሳብ ይጀምራል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት ላይ የደረሱ ጥፋቶች፣ ከእኔ እምነት ውጪ ለአሳር በሚሉ ጨለማ አስተሳሰቦች የተፀነሱ፣ በግብር ተወልደው ያደጉ ውረደቶች ናቸው፡፡ የአብዛኛዎቹ ሀይማኖቶች መፃህፍት ፍቅርን ከትበው ሳለ፤ መምህራን ነን በሚሉ፣ መፃህፍቱን ተሸክመው ከራሳቸው በሚያነቡ ሰዎች ተጠምዝዘው፣ ተከታዮቻቸውን የጥፋት መሳሪያ ሲያደርጓቸው እንታዘባለን፡፡ አብዛኛዎቹ በኢትዮጵያ ያሉት፣ ቢያንስ በጉልህ የሚታወቁት፣ ከሞት በኋላ ህይወት አለና ዘላለም ለመኖር፣ አልያም ገነትን ወይም ጀነትን ለመውረስ በመፅሐፎቻችን ቃል ማመን ይገባል የሚሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ለሌላው መልካምን ከመመኘት ሀሳብ ከተነሱ፣ በፍቅር እንጂ በጉልበት እንደምን ይኬዳል? ካልተደነቆረ በቀር፣ አያስኬድም፡፡ ደግሞስ ሰው፣ አይ የዘላለም ህይወትን አልፈልግም፣ ገነት ወይም ጀነትም ትቅርብኝ ቢል፣ መብቱ አይደለም ወይ? አንተ አምነህ መንግስተ ሰማያት ወይም ጀነት የመግባት መብትህ እንደተጠበቀ ሁሉ፣ እርሱም አላምንም ብሎ ወደ ፈለገበት የመንቀሳቀስ መብቱን ጠብቅለት፡፡ የተወለድነው ሰው ሆነን እንጂ ክርሰቲያን፣ ሙስሊም፣ አልያም ሌላ ሆነን አይደለም፡፡ ከዚያ ምርጫው የእኛ ነው፡፡

እናም አቃጣዮች፣ የሀይማኖት ተቋማትን ስታቃጥሉ፣ አገርን እያቃጠላችሁ እንደሆነ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ራሳችሁን እያቃጠላችሁ እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ በተቃጠለ ሀገር መኖር አይቻልምና!!!

bottom of page