top of page

ሀገር ማለት

በየጥጋጥጉ ሆነው የሚወራወሩ፤ ተማርን፣ አወቅን፣ ጠነቀቅን የሚሉ ነገር ግን የህሊና እንጭጮችን ባይ ይህችን ክታብ ላጋራ ወደድኩ፡፡ ሀገር ምንድን ነው፤ ገብቶናል ወይ ብዬ ጠየቅሁ…

ምንም የእኔ ሀተታ ባይመጥነውም፣ በደረስሁበት የግንዛቤ ደረጃ ሀገር ማለት ለእኔ እንዲህ ነው፤ ስሙኝ፡፡ ሀገር ማለት ዛሬ ደርሰን የፈጠርነው፣ በእኛ ትውልድ ሁሉ ነገሩ የሚሰራ ሳይሆን ዘመን አዝማናትን አልፎ እዚህ የደረሰ፤ አያት ቅድመ አያቶቻችን ደምና ላብ የከፈሉለት ዕንቁ ነው፡፡ በሰው ሀገር በነፃነት ተቀምጠን፣ በኮምፒዩተር ስክሪን በጣቶቻችን የምንሰርዝ የምንደልዘው ዕቃ ዕቃ ሳይሆን፤ የከበረ ስጦታ ነው፡፡ ሀገር ማለት ሰው የተባለ ድንቅ ፍጡር፣ ጥበብ የለበሱ አረጋውያን፣ ልበ ንፁሕ ምንም የማያውቁ ሰብዓ-መላዕክት ህጻናት የሚኖሩበት ስፍራ ነው፡፡ ሀገር ማለት ሌላው ሀገር የማይሰጠን፣ ሌላው ህዝብ የማያበድረን የእኛ የሆነ፤ በመለኮት ፈቃድ የተሰጠን፣ መርጠን ያልተገኘንበት፣ ተመርጦ ግን የተሰጠን ልዩ ጌጣችን ነው፡፡ በጣጥሰን ብንጥለው ማጌጥ የሚቀርብን እኛ እንጂ፤ ወርቅ ተበጣጥሶም ያው ወርቅ ነው፡፡ አዎን ሀገር ማጌጫ ሀብል፤ መታያ ጌጥ፤ አንፀባራቂ ማርዳ ነው፤ በደረታችን ሆኖ የሚያስከብረን፤ ከተለያዩ ብልቶች ብንገጣጠምም እንደ ሰው የሚያስጠራን ክብር ነው፡፡

ሀገር ቤት፤ ሀገር ገመና ከታች ነው፡፡ ቢሞላም ቢጎድልም ክትት ብለን የምኖርበት፤ ብንጠግም የማይተፋን፤ ብናጣም የሚችለን ቤታችን ነው፡፡ ተዘርቶ የሚቃምበት፤ ከነ ድህነትም ቢሆን ተከብረው የሚኖሩበት፤ ቀባሪ የማያጡበት ስፍራ ሀገር ነው፡፡ ሀገር ሳይኖር ጠብም ብርቅ ነው፤ ሀገር በሌለበት እንኳን ፍቅር ጦርነትም የለም፡፡ ዛሬ ከግራ ቀኝ የምንቧጨቃት ሀገር ባትኖር፤ በየምንኖርበት ሀገር ላሉ ባለሀገሮች ቀጥ ለጥ ብለን ተገዝተን መኖራችን ይቀጥላል፡፡ ሀገር ስላለች ግን ከፍቅር አልፈን ለጠብ በቃን፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ባትኖርስ፣ ሀገር ባይኖረንስ፣ ይህ ሁሉ ሲከፈት የሚውል አፍ ምን ያወራ ነበር? የክፋትና ፍጅት ለሀጭን ለማዝረብረብም ሀገር ያስፈልጋል፡፡ ታውቃላችሁ፣ በምትኖሩበት ሀገር ህዝብ ላይ ዛሬ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ምታደርጉትን ብትሞክሩ አንጠልጥለው የት እንደሚልኳችሁ…ያው ካላፈረስናት ወደ ምትሏት ሀገራችሁ ነው፡፡ እናት ናትና እየደማችም ትቀበላችኋለች፡፡

ሀገር ምድር ነው፣ ሀገር ሁሉን ቻይ ነው፡፡ በነፃነት የምንረግጥ አፈር፤ በነፃነት የምንተነፍሰው አየር የሀገር ነው፡፡ መሳያችን ያለበት፤ ስሜታችን የሚገባው፤ ሮጦ የሚደርስ፤ አቅፎ የሚያጎርስ፣ መቀነት የሚፈታልን ሀገር ነው፡፡ ህይወት አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስነ ልቡናዊም ነው፡፡ ሳንገላመጥ የምንጓዘው፣ ሳንርድ የምነራመደው በቅጥራችን ነው፣ ያ የነፃነት ቅጥር ሀገር ነው፡፡ ድንበሩን ስንሻገር የምንገዛው በባለ ቅጥሩ ህግ ነው፡፡ ባንረዳው ባንቀበልው እርሱ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጠያቂ ባለበት መታሰር የሚቻለው፤ አልቃሽ ባለበት መቀበር የሚቻለው በሀገር ነው፡፡ ክፉም ይሁን ደግ ተናግረን፣ በሰው አይን የገዘፍነው ስለ አሜሪካ አልያም አንታርክቲካ፤ ስለ ካናዳ ወይም ስለ ዩጋንዳ በፈፀምነው ገድል አይደለም፡፡ ያው ካላተራመስናት በምንለው ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር የተነሳ ነው፡፡ ተረጋጉ፤ ማፈረስ የሚጠይቀው ምንም ዕውቀት የለም፡፡ ባዶ ጭንቅላት በቂው ነው፡፡ ማቆየት ግን ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ሰው ከሆንን እናስብ፤ ልጆቻችንን ያለ ሀገር አንተው፣ ሜድትራንያን ባህር እንጂ ሀገር አይሆናቸውም፡፡

ሀገር ዛሬ በእኛ የተነሳ የሚረግፉ ነፍሳት፣ የሚቀጠፉ ህይወቶች ናቸው፡፡ ሀገር ያለ ሰው፣ ሰው ያለ ሀገር ባዶ ናቸው፡፡ ሰው ያለ ሀገር መፃተኛ፣ ሀገር ያለ ሰው ባድማ ነው፡፡ የምትቆጥሩትን ዘር፤ የምትዘበዝቡትን ዘር ማንዘር የገዛ ቤተሰባችሁ ታሪክ ይፋረደዋል፡፡ ሀሰት ነውና፡፡ ወደ ድንጋይ ዘመን የመመለስ ጉዞ ይብቃ፡፡ ሰው እያፈረሱ ህንፃ ማቆም ይብቃን፡፡ በሸቃጮች እየተነዱ፣ ቢታረዙ አልባሽ፣ ቢታመሙ ደራሽ የክፉ ቀን ጎረቤትን ደመ ከልብ ማድረግ የጨለማ ስራ ነው፡፡ እንደምን ሰው ሀገር አይኑረኝ ብሎ ይዘምታል፣ ካልታመመ በቀር፡፡ በእያንዳንዷ ረጋፊ ነፍስ ውስጥ ሀገር እየከሰመች ነው፡፡ እንመለስ፣ ሀገር ማለት ሰው፣ ሀገር ማለት ምድር፣ ሀገር ማለት ክብር ነው!!!

bottom of page