top of page
Search

ከባዱ ነገር

  • ©ጋሻዬ መላኩ
  • Aug 27, 2018
  • 2 min read

ወቅቱ አብዛኛው በሚባል ደረጃ፣ ኢትዮጵያውያን ስንቃትትለት የኖርነውን አየር በጥቂት መተንፈስ የጀመርንበት ነው፣ ከብዙ ጥያቄዎቻችን ጋር፡፡ የምፅፈው ፖለቲካዊ ትንታኔ አምሮኝ ሳይሆን፣ ወንድማዊ ምክርን በትህትና ለማስተላለፍ ሽቼ ነው፡፡ ለምን ተደሰትን፣ እንዴትና ወዘተ የመሳሰሉትን ለጉዳዩ ጠበብት ትቼ፣ ደስታችንን እንዴት እናስተዳድረው አልያም እንያዘው የሚለውን ሀሳብ ጠቆም ማድረግ እወዳለሁ፡፡

አዎን እኛ ኢትዮጵያውያን፣ በብዙ ፈተና ውስጥ ያለፍን፣ እያለፍንም ያለን ህዝብ ነን፡፡ ታሪካዊ ዳራችን ሲፈተሸ፣ እውን የሰው ልጅ ይህን መሸከም ይችላልን የሚያሰኙ የረሃብ እና የጦርነት፣ የጉስቁልናና የድህነት ታሪኮችን ተሸክመናል፡፡ ለመቀበል የሚከብዱ ጊዜያትን ያለፍነው፣ መከራን የመቻል ትከሻን በእጅጉ ስላዳበርን፣ የሰጠንም አስችሎን፣ እዚህ ደርሰናል፡፡ ከጉስቁልና ታሪካችን ትይዩ የልዕልናም ዘመን የነበረን፤ ከድካማችን አንፃር የብርታት ዘመን ሀውልቶቻችን ቆመው የሚሞግቱን ህዝብም ነን፣ ኢትዮጵያውያን፡፡ እንደምን ዛሬ ድረስ ቆየን ቢባል፣ ችግርን መሸከም ስለምነችል የሚለው ከመልሶቹ አንዱ ይሆናል፡፡ ልጆቹን በስደት፣ በረሃብ፣ በጥይት እየተቀማ ቻል አድርጎ፣ መቀነቱን አጥብቆ፣ ወደ ፀባኦት እንባውን እየረጨ የኖረ ህዝብ ነን፡፡ በእርግጥ ሀዘንን እንችላለን፤ ያዘነንም ስናፅናና፣ ለሞተበት ድንኳን ስንጥል የሚተካከለን የለም፡፡ የሀዘን ጥግን አይተናልና፣ ሀዘንን እንችላለን፡፡

የሰሞኑ ሁኔታ ግን፣ ደስታንስ እንችል ይሆን ያሰኘኛል፡፡ ነፃነትንስ እንችል ይሆን እያልኩ እብሰለሰላለሁ፡፡ ለምን ትሉ ይሆናል፣ አማን ጥያቄ ነው፡፡ በግልና ማህበራዊ ግንኙነታችን እርካታችን የተመሰረተው በምን ላይ ይሆን? በእኛ ማግኘት ወይስ በሌሎች ማጣት? ምናልባት የመጣንበት የተዛባ መንገድ ይሁን፣ አልያም ግላዊ ሚዛን አልባነት፤ ብዙ ጊዜ ከእኛ ሰላም መተኛት በላይ የሌላው መረበሽ የሚያስፈነድቀን ይመስላል፡፡ እጅግ ናፍቀን ደረስንበት ያልነውን የነፃነት አየር፣ ለምን ሌላው ይተነፍሰዋል ካልን፣ የደከምነው ራሳችንን ነፃ ለማድረግ ሳይሆን ሌላው ለማፈን ነበረ ማለት ነው፡፡ ሀሳብ ህልማችን ወደብ አገኘ ስንል፤ እኛን ሊመስሉ ያልፈቀዱን ሰዎች ምሰለኝ ብለን ግድ ካልን፣ የተፈቱ አሳሪዎች ሆንን ማለት ነው፡፡ ደስታዬን በሳቅ እገልፃለኁ ብለን፣ በእንባ ሊገልፅ የወደደውን እንደኔ ካልሳቅህ አልተደሰትክም ብለን ከተቆጣን ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ደስታችንን፣ ስሜታችን መግራት፣ በአግባቡ መያዝ ልንለምድ ያስፈልጋል፡፡ ችግር ያልጣላትን ሀገር፣ ደስታ እንዳይጥላት መጠንቀቅ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡

ሰው በደስታና በብስጭት ፅንፍ ላይ ቆሞ የሚያደርገውን ይስታል፡፡ ቆም ብሎ ዛሬ የምናገረው ነገ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን ማለት ብልህነት ነው፡፡ በስሜት ሆኖ፣ ዛሬ ማለፉ ላይቀር፣ ነገ አብሮ የሚኖርን ህዝብ በደስታ ስካር ባናቆስል፣ ባናቋስል ይመረጣል፡፡ በስሜት ጫፍ ሆነን የምንናገር የምንፅፈውን በማስተዋል ማድረግ ደስታችንን ዘላቂ ያደርገዋል፡፡ በምድራችን አንዱ ከፍቶት፣ ሌላው ደልቶት ልንኖር አይቻለንምና በሀሴት ስካር ቤት እንዳንሰብር፤ ምሰሶ እንዳንነቅል ልብ መግዛት ቡሩክ ነው፡፡ የመጣንበትን የሀዘን መንገድ ላለመድገም ደስታችን በታረቀ መልኩ መያዝ፣ በማስተዋል መራመድ ይገባል እላለሁ፡፡ ያጣጣምነው ደስታ ለሌሎች እንዲደርስ መትጋት፣ መውደድ እንጂ፣ እንደህፃናት እንቁልልጭ እያልን፣ በእጃችን ካለው በረከት ይልቅ፣ ሌሎችን በመከልከላችን እንዳንረካ ስክነት ያስፈልጋል፡፡ የእናት ደስታዋ የልጆችዋ መመሳሰል ሳይሆን፣ ከነልዩነታቸው በእቅፍዋ ማደራቸው ነው፣ የኢትዮጵያም እረፍት እንዲሁ፡፡

 
 
 

Recent Posts

See All
ጥቂት ዕውቀት

ጥቂት ዕውቀት በደል አይደለም፣ ትንሽ ትምህርት ኃጢዓት አይደለም፡፡ ጥቂት ዕውቀት አደገኛ የሚሆነው ተጨማሪ ለማወቅ ካላነሳሳ፤ የበለጠ ለመማር ካላነቃቃን ነው፡፡ ከሃይማኖት እስከ ፖለቲካ፤ ከቤተ ክህነት እስከ ቤተ...

 
 
 
ሀገር ማለት

በየጥጋጥጉ ሆነው የሚወራወሩ፤ ተማርን፣ አወቅን፣ ጠነቀቅን የሚሉ ነገር ግን የህሊና እንጭጮችን ባይ ይህችን ክታብ ላጋራ ወደድኩ፡፡ ሀገር ምንድን ነው፤ ገብቶናል ወይ ብዬ ጠየቅሁ… ምንም የእኔ ሀተታ ባይመጥነውም፣...

 
 
 
ራሳችሁን አታቃጥሉ

የፅሑፌ መነሻ ሰሞኑን ከወደ ጂግጂጋ የሰማነው አብያተ ክርስቲያናትን የማቃጠል መርዶ ነው፣ ዜና ብቻ ልለው አልሻም፡፡ ስለ ቃጠሎው እኩይነት እና አሳፋሪነት ለመናገር የተጠቂው ወገን አካል መሆንና አለመሆን መስፈርት ነው...

 
 
 

+17023272958

©2018 by Gashaye Melaku. Proudly created with Wix.com

bottom of page