ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች ©ጋሻዬ መላኩ
- ©ጋሻዬ መላኩ
- Jun 20, 2018
- 2 min read
በአፍሪቃ ቀንድ የምትገኙ ብቻ ሳትሆኑ የአፍሪቃ ቀንድ ሆናችሁ ወራሪን የወጋችሁ፣ የስልጣኔ ቀንድ ሆናችሁ አክሱም ላሊበላን ያነፃችሁ የኢትዮጵያ ሰዎች ሆይ፤ ይህን በገፀ-መፅሐፍ ወይም ፌስ ቡክ ደረት ከትቤ ላክሁላችሁ፡፡
የሰው ዘር መገኛ፣ የዓለም ህዝቦች መነሻ ነን እያላችሁ፣ የእናት ሉሲን አፅም የምታስጎበኙ፣ ዛሬ እንደ ጭራ ተሸንሽናችሁ እርስ በርስ በመጠፋፋት የገዛ ወንድማችሁን አፅም ልታስጎበኙ፣ ደምንም ለማፍሰስ እንደፈጠናችሁ ብሰማ አዘንሁ፡፡ ቀይ ባህርን ተሻግሮ መካከለኛው ምስራቅ ያስገመገመ የታላቅነት ድምፃችሁ፣ ማንም ሳይመጣ በገዛ ሀኬታችሁ አንሶ፣ የዘር ቁልል ተደፍቶበት ቢታፈን፣ ባለቤቱ ያቀለለውን የሚል የገዛ ራሳችሁን አባባል እንዳስታውሳችሁ ግድ አለኝ፡፡ ያ የጥንቱ የአንድነትና ሰንደቅ ፍቅራችሁ እንደ ጠዋት ጤዛ ሊጠፋ ዘንድ እንደተቃረበ ልብ በሉ፡፡ በረከት ተደርጎ የተሰጣችሁን ልሳን፣ አንዳችሁ ካንዳችሁ እየተማራችሁ ልትተረጉሙት እና ልታሳድጉት ሲገባ፣ በጥላቻ ደበላልቃችሁት ትባሉበት መያዛችሁ፣ ልባችሁ የዘለቀ ክፉ እንዳለ ምስክር ነው፡፡ በግዮን የተከበቡ መንደሮቻችሁ፣ በአዋሽ የተጎነጎኑ መሬቶቻችሁ፣ የእናንተን ልበ መራርነትና ቂም ተመልክተው በሀዘን ተለጎሙ፡፡ የስነ ምግባር መካናት ቤተ እምነቶች፣ በዘራፊዎችና ለመንጋው በማይራሩ ተሞሉ፡፡ እናንተም በፍቅር እና በልመና እንደማስታወቅ፣ ሁሉ ተሳዳቢ፣ ሁሉ አዋቂ ሆኖ አድማጭ ጠፋ፡፡ የሰማዩ ግን አሁንም ይናገራል፣ ወደ ፍቅር ኑ፡፡
የነገስታቱን ግፍ የሚገለብጥ፣ መሪር አገዛዝንም የሚሰብረው ኃያል ኃይል ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ይህን ብትይዙ አይደለም ለራሳችሁ፣ ከአፍሪቃ አልፎ ለዓለም በተረፋችሁ ስል አልዋሽም፡፡ እናንት የሶስቱ አብረሃማዊ እምነቶች መናኃሪያ የሆናችሁ፣ ከጥቁር ዓለም ቀድማችሁ የነቃችሁ አናብስት ሆይ፣ ኃይላችሁን በፍቅር አድሱ፡፡ ጥላቻን መከለስ፣ ወንድምን መክሰስ እንዳይረባ አውቃችሁ፣ ጎዳናዎቻችሁን በደም ሳይሆን በይቅርታ እጠቡ፡፡ በምድራችሁ ጥቂት አልጠግብ ባዮች ከትንሽ እስከ ትልቅ የብዙኃኑን ልብ እንደ ሰበሩ አውቃለሁ፡፡ እነዚህ ግን የቱንም ህዝብ አይወክሉምና ከስሜት ወጥታችሁ፣ ግለሰቦችን ከብሔር ነጥላችሁ በርትዕ እንድትዳኙአቸው ይሁን እንጂ፣ ከግፋቸው ፈንታ በሌለው ላይ አትፍረዱ፡፡ በእናንት የደረሰውን ግፍ በሌላው ብትደግሙ፣ አሁንም የጥላቻ ባሮች ትሆናላችሁና፣ ዓብይ በሆነው የፍቅር መንገድ ትመሙ፡፡ የወጋገነው ሰማይ የሚነጋው እናንተ እንደ አዕዋፍ፣ ዜማችሁም ፍቅር ሲሆን ነውና፡፡
በአራቱም ማዕዘናት መፈናቀል እና ስደት ቢሆንም፣ የተስፋችሁ ዘይት እንዳይሟጠጥ እላችኋለሁ፤ ከእናንተ ማንም ስለነገ አያውቅምና እንደ የእምነታችሁ ፀልዩ እንጂ፣ አትበቀሉ፡፡ ፀሎት ግን እጅን አጣምሮ መቀመጥ ሳይሆን፣ የለመኑትን የሚቀበል ልብን አዘጋጅቶ፣ ወደ ለመኑት እየተራመዱ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ድንጋይ ጠርበው ታሪክ ያስቀመጡ አባቶቻችሁ ዛሬ የእናንተን ዕድል ቢያገኙ ኢትዮጵያ ልትደርስ የምትችልበትን ከፍታ እያሰባችሁ፤ በፅኑ መንፈስ እና በአንድ ልብ ዝመቱ፡፡ በመካከላችሁ መለያየትን የዘራ ሊቆረጥ ዘንድ ቀኑ ቀርቧልና ከፊት ይልቅ አብዝታችሁ ተዋደዱ፡፡ የዘረኝነትና ጠባብነትን አዚም አስወግዳችሁ፣ ከምድራችሁ የራቀውን ክብር ብትመልሱ፣ ከድህነት መዝገበ ቃላት ምሳሌነታችሁን የምትፍቁበት ቀን ቅርብ ነው፡፡ ይህ ግን የይሆንልሃል ይሳካልሃል ቀረርቶ የሚያመጣው ሳይሆን፣ በላብህ ወዝ ጥረህ ግረህ ብላ እንደተባለ፣ በፅኑ ሥራ እና ተስፋ፣ እምነትና ፍቅር የሚሆን ነው፡፡ የመረጣችሁን ፍቅር ብትረዱት፣ ሰይፋችሁን ማጭድ፣ ጦራችሁን ማረሻ አድርጋችሁ ብትተጉ፣ እንደ ጥንቱ ታላቅ መሆንን የሚከለክላችሁ አንዳች አይኖርም፡፡ በፍቅር ተመላለሱ፣ ከመተላለቅ ግን ተመለሱ፡፡ ከመካከላችሁ እንደወጣ፣ ከእናንተም እንደ አንዱ እንደሆነ ይህን እላችኋለሁ፣ ከእናንተ መካከል እናት አባቱ፣ አልያም አያት ቅድመ አያቱ ከተለያየ ብሔር ያልሆነ አንድ ስንኳ አይገኝም፡፡ ከእናንተም ከሌላ ወገን ምሽትን ወይም ባልን ያለወሰደ ጥቂት ነው፡፡ ታዲያ የልጆቻችሁ ብሔር ምንድር ነው? ከምታሳንሷቸው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ንገሩአቸው፤ ስማችሁም ከተወደደች ሀገራችሁ ጋር ደምቆ ይጻፍ፡፡ በፊደል ብዛት እንዳላደክምኋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፣ የኑሮ ሩጫ ቢከብድባችሁ እያረፋችሁ አንብቡት፣ ፍቅር የራበው ቢኖር ደግሞ አካፍሉት፡፡ ፍቅር እናንተ ጋር ይሁን!!