top of page
Search

ለነገ የማይሆኑ ትናንቶች ©ጋሻዬ መላኩ

  • Writer: Gashaye Melaku
    Gashaye Melaku
  • Jun 14, 2018
  • 1 min read

ከኑሮ አንስቶ እስከ ሙዚቃ ቅኝት፣ ትዝታ በኢትዮጵያውያን ህይወት ሥፍራው ላቅ ያለ ነው፡፡ እጅግ ይወደዳል፡፡ ትናንትን መተረክ፣ በትናንት መፎከር፣ በትናንት መፅናናት፣ በትናንት መተከዝ እንደኛ የሚያውቅበት ያለ አይመስልም፡፡ እርግጥ ነው ትናንት የዛሬ መሰረት ነውና ሊዘከር፣ ሊተነተን ይገባዋል፡፡ የመጣበትን የማያውቅ የሚሄድበት ይጠፋዋል የሚለው ንግግርም አማን አለው፡፡ ከትናንት መማር እና ትናንትን መኖር ልዩነት አላቸው፡፡ የብዙዎቻችን ህይወት ፊትን አዙሮ ወደ ፊት ለመሄድ እንደመሞከር የሆነው፣ ከትናንት እየተማርን ሳይሆን፣ ከነገ ተበደርን ትናንትን እየኖርን ስለሆነ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ግለሰብም እንደ ሀገርም እየታገለን ያለ፣ በጥብቅ ያሰረን ደዌ ነው፡፡

በትናንቶቻችን ውስጥ ከፍታና ዝቅታ፣ ድልና ሽንፈት፣ ክብረት እና ቅሌት፣ ሰላምና ጦርነት ይኖራሉ፡፡ ከአሉታዎች መማር፣ አዎንታዎቹን ማዳበር የነገ ስንቅ ነው፡፡ እንደ ግል በውድቀቶቻችን ላይ ተተክለን መቅረት፣ ለነገ ዛሬ ላይ መሸነፍን ጀባ ይለናል፡፡ ተሸንፈን የምንጀምረው ለሊት በመቃብር ሆድ እንደማደር ነው፣ ሽንፈቶቻችንን ማንገስ ራስን ለትዝታ ባርነት መጣል ነው፡፡ በፅናት ለመራመድ፣ ትናንት መውደቅ፣ ዘላለም መውደቅ አለመሆኑነ መረዳት ይጠይቃል፡፡ በትናንት ጠብ ዛሬ መረበሽ፣ በትናንት ቁርሾ ዛሬ በስጋት መኖር የለብንም፡፡ ክፉውን በመልካም አሸንፈን ማለፍን ባህል ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ አዎን፣ ለነገ ከማይጠቅሙ ትናንቶች ዓይናችን ካልተነሳ ህይወት ያው፣ ዕድሜም ቁጥር ብቻ ይሆናል፡፡

እንደ ሀገርም ይኸው ነው፡፡ የደረቀን ጠባሳ ቀስቅሰው በሚያስመረቅዙ የክፋት ፀሐፍያን የትውልዱ ልብ ተበክሏል፡፡ አንድ ሆነን ሀገር ከመከትንበት ይልቅ የተላለቅንበትን፤ ከተጋባንበት የተፋታንበትን፤ ከተዋለድንበት የተፋጀንበትን ትናንት ብቻ እያጎሉ ዛሬአችንን በቂምና በጥላቻ የሚያጨልሙ አኮስሰውናል፡፡ ከጥፋቶቻችን መማር ሲገባን ጥፋታችንን በሌላ ጥፋት ካላረምን ማለታችን በውድቀት ቀለበት እየከተተን ነው፡፡ የሚሻለን ግን ፍቅር ነው፡፡ የሚያራምደን ቅንነት፣ የሚያስኬደን ይቅርታ ነው፡፡ በትናንት ውስጥ ያልበደለና ያልተበደለ የለም፤ ቂምና ቁርሾ፣ እንኳን አንድ ወዳጅ ራሳችንንም አይተውልንም፡፡ ያጠፋናል፡፡ ፍቅር ግን ያኖረናል!!! ለነገ ከማይሆኑ ትናንቶች ይልቅ ዛሬን እንጠቀም፣ ነገ ብሩህ ይሆናል!!

ለትውልዴ እፅፋለሁ!!!

 
 
 

Recent Posts

See All
ጥቂት ዕውቀት

ጥቂት ዕውቀት በደል አይደለም፣ ትንሽ ትምህርት ኃጢዓት አይደለም፡፡ ጥቂት ዕውቀት አደገኛ የሚሆነው ተጨማሪ ለማወቅ ካላነሳሳ፤ የበለጠ ለመማር ካላነቃቃን ነው፡፡ ከሃይማኖት እስከ ፖለቲካ፤ ከቤተ ክህነት እስከ ቤተ...

 
 
 
ሀገር ማለት

በየጥጋጥጉ ሆነው የሚወራወሩ፤ ተማርን፣ አወቅን፣ ጠነቀቅን የሚሉ ነገር ግን የህሊና እንጭጮችን ባይ ይህችን ክታብ ላጋራ ወደድኩ፡፡ ሀገር ምንድን ነው፤ ገብቶናል ወይ ብዬ ጠየቅሁ… ምንም የእኔ ሀተታ ባይመጥነውም፣...

 
 
 
ራሳችሁን አታቃጥሉ

የፅሑፌ መነሻ ሰሞኑን ከወደ ጂግጂጋ የሰማነው አብያተ ክርስቲያናትን የማቃጠል መርዶ ነው፣ ዜና ብቻ ልለው አልሻም፡፡ ስለ ቃጠሎው እኩይነት እና አሳፋሪነት ለመናገር የተጠቂው ወገን አካል መሆንና አለመሆን መስፈርት ነው...

 
 
 

+17023272958

©2018 by Gashaye Melaku. Proudly created with Wix.com

bottom of page